Official Site for ALEJE (Timret) | Ethiopia

ብልህ የሀገር መሪዎችና አባቶች (statesmen) በሚያስፈልጉበት የቀውስ ዘመን ጥሩ ፖለቲከኛነት በቂ አይደለም:: ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ
በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ  በዋሽንግተን ሜትሮፖሊታን አካባቢ ኢትዮጵያውያን በተዘጋጀው፣ ሼራተን ናሽናል ሆቴል ኣርሊንግተን ቨርጂንያ ፌብሪዋሪ 19  2012 በተደረገው የኢትዮጵያውያን ስብሰባ ላይ የቀረበ

የዶ/ር ብርሃኑ ንግግር በ PDF

የዛሬ ሶስት ዓመት የአሜሪካ ፕሬዜዳንት ሆነው በከፍተኛ ድምጽና በታላቅ ተስፋ የተመረጡት ባራክ ኦባማ ዛሬ የገቡበትን ኣስቸጋሪ የፖለቲካ ሁኔታ ለሚመለከት ማንኛውም ሰው (የሚቀጥለውን ምርጫ ያሸንፋሉ ኣያሸንፉም የሚለውን መላምት ለጊዜው ትተን) በፖለቲካ አለም ሶስት አመት ምን ያህል ረጅም ጊዜ መሆኑን ከመገንዘብ ባሻገር የግድ የሚጠይቃቸው ብዙ መሰረታዊ ጥያቄዎች አሉ:: ከነኝህም ውስጥ ለምሳሌ: ይህ ሁሉ ተስፋ እንዴት ባጭር ጊዜ እንደዚህ መከነ? ባራክ ኦባማ ማድረግ ያልነበረባቸውን ምን ነገር አድርገው ነው ሁሌም የሚጠሉዋቸውን አክራሪ ሪፐብሊካኖችን ማቅረብና አገሪቱ ለገባችበት ቀውስ የጋራ መፍትሄ መፈለግ እንኳን ቢሳናቸው እንደዚያ ይወዱዋቸው የነበሩትን ተራማጆችንና በተለይም ወጣቶችን ማሰባሰብና መምራት ያቃታቸው? በከፍተኛ የለውጥ ናፍቆት አብሮአቸው የነበረው ያ ሁሉ ሀይል በስርዓቱ ውስጥ ለውጥ ሊመጣ አይችልም ወደሚል ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንዴት ተመልሶ እንዲገባ አደረጉት? (ስለዚህም እንደ “ቲ ፓርቲና” “ኦኩፓይ ዎልስትሪት”ን አይነት ካሉት ፓርቲዎች ውጪ ያለ መፍትሄ እንዲፈልጉ ያስገደዳቸው?) ይህን አገር ከፍተኛ ችግር ውስጥ የከተተውና በ2008 ዓም ምርጫ ጊዜ በህዝቡ ተተፍቶ የነበረው የቡሽና የሪፑብሊካኖች የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዴት አሁን ተመልሶ እውነተኛ ተፎካካሪ ለመሆን በቃ?…ወዘተ የሚሉ አስገራሚ ጥያቄዎች ያስነሳል:: የአሜሪካንን   ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተል ሁሉ እነኝህ ጥያቄዎች በአዕምሮው ሳይመላለሱ አይቀሩም:: ብዙዎቻችሁም ለነዚህ ጥያቄዎች የራሳችሁ መልሶች እንደሚኖራችሁ እርግጠኛ ነኝ። በበኩሌ ለነዚህ ጥያቄዎች ዝርዝር ምላሽ በመስጠት ግዚያችሁን አላጠፋም። ሆኖም ከዛሬው የእኛ ጉዳይ ጋር በቀጥታ ተያያዥነት ያለው ስለሚሆን ኦባማን ለእንዲህ አይነቱ ችግር የዳረጋቸውን አንድ መሰረታዊ ጉዳይ ብቻ አነሳለሁ ።

በበኩሌ  ይህ የኦባማ መሰረታዊ ችግር  ከመሪነት ጋር የተያያዘ ችግር ነው። ኦባማ ከተመረጡ በኋላ ጥሩ ፖለቲከኛ ሆኑ:: ግን ጊዜው የሚጠይቀውን መሆን አልቻሉም:: ስልጣን ላይ ከወጡ ጊዜ ጀምሮ አገሪቱ የገጠማትን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ከእውነተኛ መሪዎች እንደሚጠበቀው በድፍረት ከመግፋት ይልቅ እንደማንኛውም ጥሩ ፖለቲከኛ የሚቀጥለውን ምርጫ በማሰብና ለዚያ ምርጫ ያስፈልጉኛል ብለው የያስቧቸውን ሀይለኛ የህብረተሰብ ክፍሎች እሹሩሩ ሲሉ የመጀመሪያውን ሁለት ወሳኝ አመታት ለእውነተኛ ለውጥ ሳይጠቀሙባቸው ቀረ:: ይህን ድክመታቸውን ያዩት የስርዓቱ ጠባቂዎችም በዚህ ድክመታቸው ተጠቅመው ከተራ ፖለቲከኞች የተለዩ ልዩ መሪ ሳይሆኑ እንደማንኛውም ፖለቲከኛ ድምጽ ቆጣሪ፤ ድምጽ ለማግኝት ደግሞ ገንዘብ የሚያስፈልገው፤ ስለዚህም የነበረውን ስርዓት በመሰረቱ ሊለውጡ ያልተዘጋጁ መሆናቸውን አረጋግጠው ሲያበቁ የተበላሸው ስርዓት ባለበት እንዲቀጥል ቀድሞ ወደነበረው አሰራራቸው ተመለሱ:: ስርዓቱ ምንም አለመለወጡን ያየው ለውጥ ናፋቂ ሰፊ ህዝብም ወደ ጥልቅ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ተመልሶ ገባ:: ሌሎች በዚህ ላይ ያላነሳኋቸው ምክንያቶች እንዳሉ ሆኖ ለዚህ ይመስለኛል ኦባማ እንዲህ ባጭር ጊዚ ሊታመን የማይችል የፖለቲካ ችግር ውስጥ የገቡት:: ችግሩን መጀመሪያውኑ የፈጠሩት ሰዎች፤ችግሩን በፈጠሩበት ፖሊሲ ላይ ተመስርተው እንደገና ስልጣኑን ለመረከብ ያቆበቆቡት:: ባጭሩ የኔ ግምት አሜሪካ እውነተኛ መሪ (statesman) በምትፈልግበት ጊዜ ኦባማ ጥሩ ፖለቲከኛ በመሆን ብቻ ቸግሯን ሊፈቱላት ባለመቻላቸው ከሳቸውም የባሱ ተራ ፖለቲከኞች ስልጣኑን ተረክበው ቀውሱን ሊያባብሱት እየተዘጋጁ ያሉ ይመስለኛል::

ይህ እኛ ኢትዮጵያውያን ካለንበት የፖለቲካና ማህበራዊ ቀውስ ጋር እንዴት ይያያዛል? በተለይ ዛሬ ልንወያይበት ከተዘጋጀነው የጋራ ትግል አስፈላጊነት ጋር እንዴት ይገጥማል?

መቼም አገራችን ቢያንስ ላለፈው ግማሽ ምዕተ አመት የገባችበትን ሁለንተናዊ ቀውስ አሜሪካ ከ2007 ጀምሮ ከገባችበት ቀውስ ጋር እንዲያው ለማወዳደር መሞከርም ሀጥያት ሳይመስል አይቀርም:: አላማዬም እሱ አይደለም:: እኛ ያለንበት ሁኔታ አይደለም ካሜሪካ በአፍሪካም ደረጃ ተወዳዳሪ የሚገኝለት አይመስለኝም:: ባለፉት ሀምሳ ግድም አመታት እንኳን የሆነውን ብንመለከት፤ በፖለቲካ ደረጃ እራሱን ከጊዜው ጋር መቀየር ያቃተው ዘውዳዊ ስርዓት ለስርዓቱ ቀጣይነት አስፈላጊ የሆኑ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ለውጦችን ለማምጣት አይደለም በራሱ በቤተሰቡ መሀከል የተረጋጋ ሽግግር ማድረግ ተስኖት ስልጣኑን በውርደት ለቅቆ አገሪቱንም የከፋ ቀውስ ውስጥ ጥሏት አለፈ:: የለውጡን እንቅስቃሴ የጀመረው ተራማጅ ሀይል ከጥቅል የለውጥ ፍላጎት ባሻገር የለውጡ ቅኝት ሶሻሊስታዊ መሆን አለበት በሚለው ሀሳቡ የአብዛኛውን ህዝብ ቀልብ የሳበና ከፍተኛ ድጋፍ ያገኘ ቢሆንም ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ምንም ባልተገናኘ፤ የትኛው አይነት ሶሻሊዝም ነው ትክክለኛው፤ እኔ ካንተ በላይ ንጹህ ነኝ፤ እኔ ነኝ እውነተኛውን ሳይንስ የምከተለው፤ ከኔ በላይ ለሰፊው ህዝብ የቆመ ላሳር ነው፤እኔ የማምንበትን አይነት ሶሻሊዝም ያልተቀበለ ሁሉ ጸረ ህዝብ ነው፣ በሚል አላዋቂና ትርጉም የለሽ ሽኩቻ ተጠምዶ፤ ከአገር ጥቅም አንጻር ብዙ ርቀት አብረው ሊጓዙ የሚችሉ ሀይሎች እርስ በእርስ ሲፋተጉ ሁሉም ተዳክመው፤ ብዙ የአገር አይን የሆኑ ዜጎችን ገብረው፤ ሜዳውን ምንም ችሎታም፣ ለከትም ለሌለው ወታደራዊ ሀይል ለቀቁለት:: በመንግስቱ የሚመራው ወታደራዊ ሀይልም ታሪክ የሰጠውን፤ ኢትዮጵያን በአዲስ መልክ የመቅረጽ እድል አፈር አስገብቶ ስልጣን አለመልቀቅን ማዕከል ባደረገ የአጭር ጊዜ ስሌትና፤ ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ እንዲሉ፤ ከኔ በላይ ሶሻሊስት፤ ከኔ በላይ ለአገር ተቆርቋሪ ላሳር ነው፣ በሚል የጅል ግብዝነት፤ ጠንቅቆ ካለማሰብ የሚመጣ ያላዋቂ ድፍረትና ጭካኔ ተጨምሮበት፤ ምድሪቱን የደም ምድር አደረጋት:: በብልሀትና በትዕግስት ሊፈቱ የሚችሉ ማህበራዊ ቅራኔዎችን አጋኖና በሞኝ የአገር ፍቅር አክራሪነት ለጥጦ ሊፈቱ በማይችሉበት ሁኔታ አጦዛቸው:: ከ17 አመታት የፍርሀትና የሽብር አገዛዝ በኋላ ከጣለው ኋላ ቀር የዘውድ አገዛዝም ያነሰችና የተተራመሰች ኢትዮጵያን ትቶ፤ በስልጣን ዘመኑ የሰበሰባቸውን ብዙ አድር ባዮችና አንዳንድ በዓላማው አምነው የተቀላቀሉትን የዋሆች ሜዳ ላይ በትኖ፤ ከኔ በላይ የአገር ፍቅር የሚያቃጥለው፤ ከኔ በላይ ጀግና የለም ይል የነበረው መሪ፤ በሱ እውር ጭካኔ ምክንያት አንገቱን የደፋውን ህዝብ ፈሪ ብሎ ሰድቦ መለስና ወያኔን ስልጣን ወንበሩ ላይ ትቶ ቤተሰቡን ብቻ ይዞ ተሰደደ:: እውነተኛ የሀገር መሪ በማጣት የተበላሸ የመጀመሪያ የታሪክ አጋጣሚ::

ይህን ሁሉ ትርምስ ያየ ከታሪክ ይማራል፤ ሌሎች የሰሩትን ስህተት አይደግምም፤ ቢያንስ ለራሱ ታሪክና ለዓላማ ብለው ለሞቱት ጓዶቹ  ክብደት ይሰጣል፤ ተብሎ ሲጠበቅ አሁንም ታሪክ ባጋጣሚ የሰጠውን ጥሩ ታሪክ የመስራት እድል ለዘመናት ሆዱ ውስጥ ተሸክሞት ሲዞር ለነበረው ቂምና ጥላቻ፤ እልህና ስግብግብነት፤ ከበታችነት ስሜት ጋር ተያይዞ የሚመጣ የተሻለው የሚመስለውን አጭበርብሮና አሰገድዶም ቢሆን ለመብለጥ አልያም ለማዋረድ ለሚፈልግ  ወደር ለማይገኝለት ትንሽነት ለወጠው:: ባለው ላይ ለመገንባት፤ በጎደለው ለመጨመርና ወደፊቱን ለማሻሻል ከመሞከር ይልቅ፣ ለትንሽነቱ ምክንያት አድርጎ የወሰደውን የአገሪቱን ታሪክና ማንነት ማንኳሰስ፤ አገራዊ ተቋሞቿን ማጥፋት፤ የጥላቻ ስሜት ዘር መዝራት፤ የህዝቧን አንድነት ሆን ብሎ ማደፍረስን ስራዬ ብሎ ተያያዘው:: የብሄሮች እኩልነት ዋና መመሪያዬ ነው እያለና በብሄር ካልሆነ መደራጀት፤ ስለኢትዮጵያዊነት ማውራት፤ እራስን ኢትዮጵያዊ ብሎ መፈረጅ የትምክህተኝነት መገለጫ ነው ብሎ እየተመጻደቀ፤ ዘውጌ ብሄረሰቦች ያለሱ ቡራኬ በነጻነት እንዳይደራጁና እንዳይንቀሳቀሱ ከለከለ:: ለእሱ ጭቁን የሚላቸው ብሄረሰቦች በነጻነት ተደራጅተው በነጻነትና በእኩልነት የሚኖሩ ነጻ ህዝቦች ሳይሆኑ እሱና ምርጦቹ ዝለሉ ሲሏቸው ስንት ከፍታ እንዝለል የሚሉ የእሱ የከፋፍለህ ግዛው መሳሪያዎች ሊያደርጋቸው ፈለገ::

አገሪቱ ከብዙ ግጭቶች ገና መውጣቷ ነው፤ ሌላ የፖለቲካ ግጭት ውስጥ መግባት የለባትም ብለው በሰላማዊ መንገድ፤ አንተው ባወጣኀው ህግ መሰረት፤ የህዝቡን መብት አክብረህ አስተዳድረን ያሉትን የፖለቲካ ተቃዋሚዎች፤ ጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋቾች የሚያሳዩት የሞራል ትልቅነትና የውስጥ ድፍረት የራሱን የፈሪነት ስሜት እያስታወሱት ነው መሰል ፈሪ በመሆናቸው መራራ የጉልበት ትግል ውስጥ የማይገቡ፤ ህዝቡም የፈለገውን ቢያደርገው ፈጽሞውኑ የማይነሳ ፈሪ ህዝብ አድርጎ ለመግዛት ወሰነ:: ይህ ከፍርሃት የመነጨ ትዕቢት አቅፎና ደግፎ ለስልጣን ያበቃኝ የቁርጥ ቀን ወዳጄ ነው የሚለውን ገበሬ እንኳን ከስልጣን በኋላ ወዳጁ ሊያደርገው አልቻለም:: የመሬትህ ባለቤት ከሆንክ ያንተው አገር ብልጥ ባለሀብቶች በገንዘብ አታለውና አጭበርብረው (ላንተ ገንዘብ  ሰጥተው) ይወስዱብሃል፤ ስለዚህ የኔ ጭሰኛ እንደሆንክ ብትቀጥል ይሻልሀል በሚል ተራ “ወዲ ሹቅነት” አታሎና አስገድዶ ለማኖር ብዙ ጥረት አድርጓል። ይህም አልበቃ ብሎት  የዚህኑ ድሀ ገበሬና አርብቶ አደር መሬት ያለፍላጎቱ፤ በልማት ስም፤ ከእሱ በፊት የነበሩትን ገዢዎች ፍጹም የተቀደሱ  በሚያስመስል መልክ፤ የማይጠረቃ የነዋይ ፍቅሩን ለማሟላት ሲል ብቻ የአገሪቱንና የህዝቡን መሬት ለባዕዳን ባለሀብቶች በጣም ባነስተኛ ገንዘብ ቸበቸበው:: ገሚሱን መሬት ደግሞ ድንበሩን ከተቃዋሚዎቹ የአገሩ ልጆች እንዲጠብቁ በሚል ሰፊ ያገሪቱን መሬት ለባእዳን የጅ መንሻ አቀረበው:: በዚህም ገበሬውንና አርብቶ አደሩን በገፍ አፈናቀለው::

ድሮውንም ከእጅ ወደአፍ ይኖር የነበረውን ድሀ፤ ጥቂት ምርጥ ቡችሎቹን በአቋራጭ ለማበልጸግና በእሱ አምሳያ የተፈጠረ፤ ምንም የሞራል ለከት የሌለውን አዲስ የገዢ መደብ ለመፍጠር በሚል ሆን ብሎ በጀመረው የገንዘብ ህትመት በፈጠረው የዋጋ ግሽበት በአገሪቱ ታይቶ የማይታወቅ የድህነት አረንቋ ውስጥ ከተተው:: ጃንሆይም ሆነ ደርግ በትንሹም ቢሆን እየፈጠሩት የነበረውን የመካከለኛ ገቢ መደብ በዋጋ ንረት ድራሹን አጥፍቶ አገሪቱን የጥቂት የናጠጡ ባለሀብቶችና ሌላው ሁሉ ድሀ የሆነባት የምድር ሲዖል አደረጋት:: በዚህ መልክ ከአገሩ ህዝብ የሚሰበስበው ግዙፍ “የዋጋ ግሽበት ታክስና” ከመሬትና ከአገር ሀብት መቸብቸብ የሚገኘው ገንዘብ ስላላጠረቃው፤ አልፎም “ለክፉ ጊዜ” የሚያሸሸው የውጭ ምንዛሪ ስላስፈለገው፤ ለስልጣን ያበቁትን ታጋዮችና አገር የጠበቁ መስሏቸው ወታደር የሆኑ ወጣቶችን በቀላጤ እያዋጋና እያስጨረሰ እነሱ ለሞቱበት እሱ የውጭ እርዳታና ክፍያ ይሰበስባል:: ምንም እፍረት የማይሰማው እኩይ ሀይል ስለሆነ ባለፈው ዘጠኝ ዓመት ብቻ እሱና ጀሌዎቹ ያሸሹት 11.6 ቢሊዮን ዶላር አልበቃ ብሎት ከዚህም በላይ አገኝ እንደሆነ በሚል በእሱው ምክንያት ከአገር ተሰደው ላባቸውን አፍስሰው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን አገር በማጥፋት ጥረቱ እንዲተባበሩት ገንዘብ አዋጡ ብሎ ሊያጃጅላቸው ይከጅላል::

እንዲህ ኣይነት አይን ያወጣ ጉድ ትንሽም ቢሆን የሞራል መሰረት ባለው አገርና በግብረገብነት የታነጹ ለእውነትና ለፍትህ የቆሙ የሀይማኖት አስተማሪዎች፤ በምርምራቸው ትክክል የሆነንና ያልሆነን መለየት የሚችሉና ትክክል ለሆነው ነገር ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩ ምሁራን በበዙበት አገር በዘላቂነት ሊቀጥል እንደማይችል ስለሚገነዘብ ይህንን የሞራል መሰረት ለመናድ የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ በስፋት ተንቀሳቀሰ::  ለፍትህና ለህግ ትልቅ አክብሮት ያለውን ህብረተሰብ ፍጹም ለማዋረድና “ከኔ ጅራፍ ማንም የሚያድንህ ሀይል የለም” የሚል አቅመቢስነት ስሜት ውስጥ ለመክተት የፍትህ ተቋማትን ፍጹም ሽባ አድርጎና ዳኞችን ለሙያቸው ቅንጣት ክብር የሌላቸው ተራ ተላላኪዎች  አድርጎ አዋረዳቸው:: ራሱን ለገንዘብ ለመሸጥ ያመቻቸውን በገንዘብ ይገዛዋል:: በግብዝነት ለስልጣን የሚያጎበድደውን ያስጎበድደዋል:: የሀይማኖት ተቋሞችን ውስጣቸው ገብቶ ይከፋፍላል፤ ለሱ የሚገዙትን አድርባዮችና ምንም የሞራል ለከት የሌላቸውን የተቋሞቹ መሪዎች አድርጎ ይሾማል:: ግብዝ ሽማግሌ ነን ባዮችን የጥቃቱ መሳሪያ በማድረግ አገሪቱ የተከበረና የታመነ አስታራቂ ሽማግሌ እንኳን እንዳይኖራት ያደርጋል:: ይህን ሁሉ ሲያደርግ ሀይ ብሎ የሚያስቆመው ስላጣ፤ ብልግናውን እንደ እውቀትና ብልህነት፤ የሰውን ዝምታ የሱን አሸናፊነትና አልበገር ባይነት ማረጋገጫ አድርጎ በመውሰድ በገባበት ለከት ያጣ የድንቁርና ትዕቢት ምክንያት ልክ ለሱ የሚበጀውን የፖለቲካ አመለካከት ከውጭ ኮርጆ ባሰለጠናቸው ጥራዝ ነጠቅ ካድሬዎች እንደሚያስፋፋው፤ ሀይማኖትን የመሰለ ትልቅ ነገር እንደዚሁ ከውጭ አስመጥቶ፤ እነኝህኑ የፖለቲካ ካድሬዎች በለብለብ አስጠንቶ የአማኙ ማህበረሰብ ጉሮሮ ውስጥ በግድ ሊሸነቁረው እየከጀለ ነው::  አማኙ ማህበረሰብ እሺ ካለው ይህን በጉልበት ከመተግበር እንደማይመለስ ለአንዳፍታም አትጠራጠሩ::

በኣጭሩ ይህ ስርአት ከቀድሞዎቹም አገዛዞች በባሰ አገር እያጠፋ ያለ እርኩስ አገዛዝ ነው:: እያንዳንዱ በስልጣን የሚቆይበት ቀንና ሰአት ኣገራችንን ለመቅበር እየቆፈረ ያለውን ጉድጓድ ጥልቀትና ስፋት እየጨመረ የሚሄድበት መሆኑን ለአንድ አፍታም መዘንጋት የለብንም:: የሚበቃውን ጊዜ አግኝቶ የጉድጓዱ ጥልቀት አገራችን ልትወጣው የማትችለው ደረጃ ላይ ሲደርስ ግን በአገርና በህዝብ ላይ ለደረሰው ከፍተኛ ጉዳት ጉድጓዱን የቆፈረው ከይሲ ብቻ ሳይሆን ይህን ጉድጓድ ጊዜውን ወስዶ ሲቆፍር ዝም ብለን ያየነው ሁሉ እንደምንሆን በዚህ አጋጣሚ በአጽእኖት ተናግሬ  ማለፍ እፈልጋለሁ:: ስለዚህ ይህ ወንበዴ ስርአት በምንም መልኩ መወገድ አለበት ብቻ ሳይሆን ባስቸኳይ፤ ምንም ጊዜ ሳይሰጠው መወገድ አለበት:: እውነተኛ የአገር መሪ በማጣት የተበላሸ ሁለተኛ የታሪክ አጋጣሚ::

መወገድ አለበት ማለት ግን፤ አንዳንድ የዋሆች እንደሚያስቡት ዝም ብሎ በራሱ ይፈርሳል፤ ከራሱ ውስጥ በመነጨ ፍላጎት ይለቃል፤ ወይንም አሁን በቅቶኛል፤ የዘረፍኩትን አርፌ ልብላ ብሎ ቀስ ብሎ ገሸሽ ይላል ማለት አይደለም:: እመኑኝ ነው የምላችሁ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ቅንጣት ታክል የውስጥ ስሜትና የራስ ክብር ቢኖረው ኖሮ በምርጫ 97 ሲሸነፍ በክብር ይለቅ ነበር:: ስለዚህ ይህንን ስርአት ማስወገድና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርአት የመፍጠር የታሪክ ሀላፊነት ያለው፤ ለዚያች አገር ቅን የሚያስቡና ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የቆሙ፤ ለዚህ ስርአት መመስረትም ምንም አይነት መስዋእትነት ለመክፈል የተዘጋጁና ይህንንም በወሬ ሳይሆን በተግባር ለማዋል የቆረጡ የቁርጥ ቀን ልጆቿ ላይ ነው:: ጥያቄው አገራችን የገባችበትን ችግር ጥልቀት በቅጡ የተረዱ  ልጆች ኣሏት ወይ? ይህን ትግል ዳር የሚያደርሱ አርቆ አስተዋይ ልጆች አሏት ወይ? ይህንን ለማድረግ የሚቻላቸው ከራሳቸውና ከጠባብ ድርጅታዊ ጥቅም ባሻገር መመልከት የሚችሉ የፖለቲካና የሲቪክ ማህበረሰብ መሪዎች አሉ ወይ? ይህን ከዳር ለማድረስስ የሚያስፈልገውና ሁላችንም የምንጋራው ራዕይ፤  የሞራል ስብዕና፤ የአደረጃጀት ብቃትና ድርጅታዊ ባህል ምን አይነት ነው? የሚለው ነው:: ከዚህ ቀጥዬ ይህንን ርዕስ በአጭሩ እቃኛለሁ::

ይህን ንግግር ስጀምር ባራክ ኦባማ የገቡበት የፖለቲካ ችግር ጊዜው እውነተኛ የአገር መሪዎች (statesmen) በሚፈለግበት ጊዜ ዝም ብሎ ጥሩ ፖለቲከኛ በመሆናቸው ነው የሚል መላምት ሰንዝሬ ነበር:: የአሜሪካው ፖለቲካ ትንተናዬ ባይስማማችሁም ግን ኢትዮጵያችን ከገባችበት ጥልቅ ችግር ለመውጣት ዝም ብሎ ተራ የዘወትር ፖለቲካ የሚያውቅ ፖለቲከኛ በፍጹም እንደማይበቃት የምንጣላ አይመስለኝም:: የእዚያ አይነት ፖለቲከኞች ደግሞ እጥረት ኖሮብን አያውቅም::  በአገራችን ለዘመናት የቆዩትንና ጊዜው በረዘመ ቁጥር እጅግ እየተወሳሰቡ የሄዱትን የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ፤ ማህበራዊና ይበለጥም ደግሞ የተጣባትን የሞራል ክስረት ችግሮቹዋን ዘላቂ የሆነ መፍትሄ የሚፈልጉላት የፖለቲካ፤ የሀይማኖት፤ የእውቀት፤ የሲቪክ መሪዎች እንደሚያስፈልጓት ጥርጥር የለውም:: ሁሉም ግን ከሚመሰረተው የፖለቲካ ስርዓት ጋር የተያያዘ ስለሆነ ለዛሬ በፖለቲካው ዙሪያ ላተኩር:: ምን ኣይነት ድርጅቶችና መሪዎች ናቸው የአዲሲቷ ኢትዮጵያችን እውነተኛ አዋላጅ መሪዎች (founding statesmen) የሚሆኑት? ከፊታችን የተደቀነውን በእኛ ህይወት እንኳን ሶስተኛ የታሪክ አጋጣሚ እንደገና እንዳይበላሽ ካለፈው የተማረ፤ ወደፊቱ ላይ ያተኮረ ያመራር አቅምና የሞራል ጥንካሬ አለ ወይ?

የአዲሲቱ ኢትዮጵያ አዋላጆች ምን መሆን ይጠበቅባቸዋል?

የአገራችንን ጥልቅ ችግር ለመፍታት አገር አዋላጆች ያስፈልጓታል የሚለው አመለካከቴ ትንሽም ቢሆን እውነትነት ከአለው፤ እንዲህ አይነት መሪዎች ወይም ድርጅቶች አሁን ካለንበት ሁኔታ አንጻር ሊኖራቸው የሚገባው ችሎታ ምን ይመስላል የሚለውን በመጠኑ ልዳስ:: ይህ ዳሰሳ ግን የአሉንን አንዳንድ ማህበራዊ ጥንካሬዎች በመርሳት ሳይሆን በችግሩ ላይ ለማተኮር በመፈለግ ነው::

በእኔ እምነት የመጀመሪያው አስፈላጊ ቸሎታ የችግሩን ጥልቀትና ውስብስብነት በውል መረዳታቸው ነው:: ችግራችን ዘርፈ ብዙ ነው:: እጅግ የሚዘገንንና የሚያሳፍር ድህነት ወሮናል:: በዛሬ ዘመን በጣም ትንሽ የሚባለውን ከማንኛውም እንሰሳ ጋር የምንጋራቸውን መሰረታዊ ፍላጎቶች እንኳን ማሟላት የማይችለው ከግማሽ በላይ ህዝባችን ነው:: ጥልቅና የተራዘመ ድህነት ሲበዛ ድሀ በሆኑት ግለሰቦች ላይ ብቻ ሳይሆን በማህበረሰቡ የሞራልና የስነልቦና ድባብ ላይ የሚጥለው ጠባሳ ቀላል ኣይደለም:: ስልጡን ሰዎች እንደሚሉት የሰለጠነ ሰው ስብእናው የሚመዘነው በነጻነቱ አድማስ (በነጻነት ማሰብ፤ በነጻነት መስራት፤ መወያየት፤ መጻፍ፤ ማምለክ…ወዘተ) ስፋት ከሆነ እንደ ህዝብ የእዚያን አይነት ስብእናን እስካሁን ኣናውቀውም:: የሰው የመረጃ ምንጭ በአብዛኛው የመንግስት መገናኛ ብዙሀን በሆነበት አገር፤ ሁሌም የሚሰማው ነገር ውሸት በሆነበት አገር፣ ተወልደን በማደጋችን እውነትና ሀሰትን ለመለየት የሚችለው የአዕምሮአችን ክፍል የሀሰት ጭጋግ የሸፈነው ይመስላል:: ለአገዛዛቸው እንዲመቻቸው ብለው በመሀላችን የነሰነሱት የመለያየት መርዝና በአብዛኛው በግማሽ እውነት ላይ ከተመሰረተው የራሳችን የማንነት ግንዛቤ ጋር ተዳምሮ፤ የገዢዎቻችን ሴራ መሆኑን እንኳን እየተገነዘብንም እርሱን በጥሰን እርስ በርሳችን ከመናቆር አልተቆጠብንም:: ለማንኛውም ጠንካራ ማህበረሰብ እጅግ አስፈላጊ የሆነው መተማመን የሚባለው ማህበራዊ ወረት (social capital) ተሟጦ ያለቀበት ሁኔታ ላይ ነው የምንገኝው:: ምክንያቱ ምን እንደሆነ ገና በቅጡ ባልገባኝ ምክንያት አብዛኛዎቻችን የአሁኑና የወደፊቱ ላይ ከማተኮር ይልቅ ባለፈው ላይ ስንራኮት ጉልበታችንንም ቅን ልቦናችንንም አብረን እንበላዋለን:: ችግር መፍታት (problem solving) ላይ የሚያነጣጥረው ያዕምሮአችን ክፍል እንዳለም እረስተን  ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ስለችግሩ ሌት ተቀን በማውራት ብቻ እረክተን ለመኖር  የመረጥን ነው የሚመስለው:: ይህ መተማመን ማጣትና መፍትሄ ተኮር ያልሆነ አካሄዳችን የጋራ ኑሮአችንን፤ፖለቲካችንን ጨምሮ፤ በዘዴ መምራት አላስቻለንም:: ከዚህም በላይ ብዙ ማለት ይቻላል:: ግን ለማነሳው ውይይት ይህ በቂ ነው::

እንግዲህ እነኝህን ሁሉ ችግሮች ከግምት ያስገባ፤ እነኝህ ችግሮች የሚፈጥሩትን የተለያዩ እንቅፋቶች መፍታት የሚችልና ማህበረሰቡን በአብዛኛው ማሰባሰብ የሚችል ራዕይ ያነገበና ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የሚችል ሀይል ነው የሚያስፈልገን ማለት ነው:: ይህ ማለት እንግዲህ ኣዲሲቷን ኢትዮጵያን ለማዋለድ የሚችሉት መሪዎች የመለስን ወራዳ አገዛዝ መጣል ብቻ ሳይሆን ከዚያ በኋላ የሚመጣው ምን መሆን እንዳለበት በጥልቀት ያሰቡበት፤ ለዚያም የሚያስፈልገውን ማህበራዊ፤ ፖለቲካዊ፤ ስነልቦናዊ፤ ተቋማዊና የሞራል ንጽህና ለመገንባት የተዘጋጁና ለዚህ የሚያስፈልገውን ሰፊ ማህበራዊ ጥምረት (broad social coalition) መፍጠር የሚችሉ መሆን አለባቸው:: መለስንና በአካባቢው የሰበሰበውን የዘራፊ ቡድን ማንበርከክ የመጀመሪያው አስፈላጊ ስራ እንጂ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ምስረታ ፍጹም በቂ እንዳልሆነ የተገነዘቡ መሆን አለባቸው ማለት ነው:: ይህ ደግሞ ምን ያህል ከባድ ስራ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም:: የብዙ ችሎታዎች ጥርቅም (skill set) ነው የሚያስፈልገው:: አላሚዎች መሆን አለባቸው:: የዚያኑ ያክል ግን መሬት የረገጡ መሆን ይገባቸዋል:: ጠንካራ የመርህ ሰዎች መሆን ይጠበቅባቸዋል:: የዚያኑ ያክል ግን የተግባር ሰዎች ሆነው የሚቻለውንና የማይቻለውን ለይተው በሚቻለው ላይ ማተኮር አለባቸው:: ብዙውን የማህበረሰብ ክፍል ለማሰባሰብ የሚያስችል ሆደ ሰፊነትና ብልሀት አስፈላጊ እሴቶች ናቸው:: የዚያኑ ያክል ግን ሁሉንም ማስደሰትና ማሰባሰብ እንደማይችሉ ተረድተውና ስራው ተግባራዊ እንደሆነና ከፍተኛ መተማመንን የሚጠይቅ መሆኑን አውቀው አብረው ሊሰሩ የሚችሉትን በጥንቃቄ መምረጥ ይጠበቅባቸዋል:: ለጊዜያዊ ውጤት የማይቸኩሉ አስበው የሚንቀሳቀሱ መሆን የሚገባቸውን ያክል የገጠማቸው ስራ ጊዜ የማይሰጥና በቶሎ መደረግ ያለበት መሆኑን የተረዱ ያስቸኳይነት ስሜት የሚሰማቸው (sense of urgency) መሆን ይገባቸዋል:: የሚታገሉት አንድን ጊዜያዊ ጠላት ብቻ እንዳልሆነ፤ በጣም የከረመ የታሪክ ዝግንትል ጥርቅም መሆኑን የተገነዘቡ፤ ስለዚህም በአንድ ቀልጣፋና ሁሉን የሚመልስ የአይዲዎሎጂ ቁልፍ የሚፈቱት አለመሆኑን ቢገነዘቡም፤ በችግሮቹ ጥልቀትና ስፋት ናላቸው ዞሮ (overwhelmed)፤ የችግሮችን ቅደም ተከተል አስቀምጠው የሚችሉትን እየፈቱ ለመሄድ የሚችሉ የገቢር ሰዎች ሊሆኑ ይገባል:: ይሄን ዝርዝር ስታዩ ሰው ሳይሆን ፈጣሪ ብቻ የተጎናጸፈው ችሎታ ሳይመስላችሁ ኣይቀርም:: በእርግጥም ይህ ሁሉ ችሎታ ያለው አንድ ሰብዓዊ ፍጡር ይገኛል ማለት ኣይቻልም:: ብዙ ሆነው ግን ሊሰሩት ይችላሉ:: መደራጀትም የሚያስፈልገው ለዚህ ነው:: ይህንን ውይይት ትንሽ መሬት ለማስረገጥ በሚል የድርጅትን ጉዳይ በምሳሌነት አንስቼ ለማሳየት ልሞክር::

ምን ኣይነት ድርጅት ወይም የድርጅቶች ህብረት ይህን አላማ ያሳካልናል?

የስራው ብዛትና የሚፈልገው ችሎታ በአንድ ወይንም ጥቂት ልዩ መሪዎች የሚሰራ አይነት አይደለም፤ ስለዚህም በጥሩ ሁኔታ መደራጀት ያስፈልጋል ከአልን ምናልባት አሁን አገራችን ባለችበት ሁኔታ አንድ ድርጅት ሳይሆን የተለያዩ ድርጅቶችን ጥምረት የሚጠይቅ መሆኑ አይቀሬ ሊሆን ይችላል:: ይህ ግን መፍትሄ ሊሆን የሚችለውን ያክል ብዙ ችግሮችን በእቅፉ ውስጥ ያዘለ ነው:: በቀጥታ ከዛሬ ጉዳያችን ጋር ስለሚያያዝና እግረ መንገዴንም ጥምረታችን ይህንን ጉዳይ እንዴት አትኩሮት ሰጥቶ እንደተመለከተው ለማመላከት ይህንን ጉዳይ ትንሽ ልሂድበት::

የተለያየ አመለካከት፤ የተለያየ የህብረተሰብ ፍላጎትን ማዕከል አድርገው የተቋቋሙ ድርጅቶችን በጋራ አምጥቶ ለጋራ እንቅስቃሴ ማሰለፍ የዋዛ ስራ እንዳልሆነ ከቅርብ ግዜ ታሪካችን ያየነው ነው:: ከላይ በማህበረሰባችን ውስጥ ተከስተዋል ያልኳቸው የተለያዩ ችግሮች ደግሞ ይህንን ጉዳይ የበለጠ ውስብስብ ያደርጉታል:: የመጀመሪያው ችግር የድርጅቶቹን አላማ የማቀራረብና ወደ አንድ ሁሉን ወዳቀፈ ራዕይ የማምጣት ስራ ነው:: ይህ ደግሞ ስላወሩት ወይንም በፐሮግራማቸው ስላሰፈሩት ከልባቸው ተግባራዊ ለማድረግ ይፈልጋሉ ማለት ላይሆን ይችላል:: ሊደርሱበት በሚፈልጉበት መዳረሻ (የራዕዩ ተግባራዊ መገለጫ) ላይ ደግሞ ልብ ለልብ ካልተገናኙ አብሮ የመጓዙ ነገር የሚሆን ኣይደለም:: ለምሳሌ የፖለቲካ ድርጅቶች በአንድ የአይዲዮሎጂ እምነት ላይ የተመሰረቱ የአንዱን መደብ ጥቅም ለማስጠበቅ የተቋቋሙ ሊሆኑ ይችላሉ:: ሌሎች ደግሞ የተወሰነን ዘውጌ ማህበረሰብ የተለየ በደል ለማካካስ ወይንም በተለይ ይገባዋል ብለው የሚያስቡትን ጥቅም ወይም መብት ለማስጠበቅ በሚል ሊመሰረቱ ይችላሉ:: ሌላው በሀይማኖት ዙሪያ ላሉ ክስተቶችና መብቶች የበለጠ አጽንኦት ሰጥቶ የተቋቋመ ማህበራዊ ወይም ፖለቲካዊ ስብስብ ሊሆን ይችላል:: አንዳንዱ በአፈጣጠሩ በአንድ አይዲዮሎጂ መሰረት ላይ ሆኖ ያንን አይዲዮሎጂ መከተሉን ከተወም በኋላም በራሱ ልዩ ድርጅታዊ ታሪክና ይህም በሚፈጥረው የአንድነት ስሜት ምክንያት ልዩ ኣደረጃጀቱን እንደያዘ የቀጠለ ሊሆን ይችላል:: ታዲያ በዚህ አይነት የተለያዩ መነሻዎች ምክንያት የተቋቋሙና የራሳቸውን ድርጅታዊ ልዩነት በቅንዓት የሚጠብቁ ሀይሎች በምን ራዕይ ዙሪያ ነው መሰባሰብ የሚችሉት? በቀላሉ መገመት እንደሚቻለው የዚህ አይነት ስምምነት ሊመሰረት የሚችለው በመሰረታዊ እምነት  (substantive beliefs) ደረጃ አይሆንም:: ሊሆን የሚችለው በአብዛኛው በሂደቱና በአካሄዱ ፍትሀዊነት (procedural justice) ላይ ነው::[1] በርግጥ ይህ ፍትሀዊ አካሄድ ከጀርባው ይዞት የሚመጣው መሰረታዊ እምነት አለ:: ይህ ግን ቢያንስ አሁን ባለንበት ዘመን እጅግም አከራካሪ ስላልሆነ በግልጽ ላያጣላ ይችላል:: ነገርዬው ግን ከአፍ ድጋፍ የበለጠ ጥልቅ ግንዛቤም ድጋፍም (committment) ይጠይቃል::

ይህ የሂደት ስምምነት ምንድን ነው? መነሻው ማህበረሰቡ መሰረታዊ በሆኑ ብዙ ጉዳዮች ላይ ልዩነት ያለው መሆኑን ከመቀበል ይጀምራል:: እንዲህ ኣይነት ልዩነቶች ያሉት ማህበረሰብ ሁሉም እንደ ግለሰብ ወይንም እንደ ልዩ ስብስብ (የባህል፤ የሀይማኖት፤ የቋንቋ …ወዘተ) በየፊናው የሚሰራቸውና ይህንንም ለመስራት የሚያስችሉት መብቶች ከተቀመጡለት በኋላ ለሁሉም የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ግን ውሳኔዎችን እንዴት እየሰጠ ይሄዳል? ምን ኣይነት የውሳኔ ኣሰጣጥ ሂደት ቢከተል ነው አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ፍትሃዊ ነው ብሎ የሚቀበለውና ለውሳኔዎቹም በግዴታ ሳይሆን በውዴታ ተገዢ የሚሆነው? ለዚህ ጥያቄ የመጀመሪያው መልስ፣ አብዛኛው ህዝብ በቀጥታ ወይም በሁነኛ ወኪሎቹ አማካኝነት የሚወስናቸው ውሳኔዎች ናቸው ተቀባይነት ያላቸው (legitimate) የሚለው ነው:: ይህ ማለት ግን አብዛኛው የሚወስናቸው ውሳኔዎች ሁልጊዜ ትክክል ናቸው ማለት አይደለም:: አንድም ስህተቱን ለማረም የተሻለ እድል እንዲኖረው የሚያስችሉ ተቋሞች (ለምሳሌ ነጻ ሚዲያ፤ ነጻ የፍርድ ተቋም…ወዘተ) በአካባቢው ከተመሰረቱ ስህተቶቹን መቀነስ፤ ሲከሰቱም ማረም ይችላል በሚል ስሌት ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ወሳኝ የሆኑ መብቶችን ከብዙሃኑም ውሳኔ ለመጠበቅ የአናሶችን መብቶች የግድ ማስከበሩ ላይ አጽንኦት መስጠቱ ነው:: ከዚያም በላይ ግን ከዚያ የተሻለ ምንም ሌላ አማራጭ ስለሌለ ነው:: ይህ አካሄድ ትንሽ እንኳን ትርጉም የሚኖረው ደግሞ ህዝቡ ፍላጎቱን የሚገልጽበትም ሆነ ወኪሎቹን የሚመርጠው ያለምንም ፍርሃትና ተጽዕኖ ሲሆንና ምርጫውም በምንም ምክንያት አለመዛባቱ ሲረጋገጥ ነው:: እነኝህን መስፈርቶች ያሟላ ውሳኔን ደግሞ (በውሳኔው ዙሪያ አለመስማማት እንኳን ቢኖር)፤ በውሳኔው ደጋፊዎችም ሆኑ ተቃዋሚዎች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል:: በዘወትር አነጋገር ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የምንለው ይህንን ነው:: በዚህ ሂደት ብቻ ውክልና ያገኝ መንግስት ተቀባይነት እንዳለው፤ ከዚህ ሂደት ውጪ የሚመጣ ምንም ኣይነት ስልጣን፤ በየትኛውም የስልጣን እርከን እንደማይኖር መስማማት ለምንም አይነት የትብብር ምስረታ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ነው:: ይህንን ከልባቸው የተቀበሉ ድርጅቶች ኣብረው ለመስራት የሚያስችላቸውን አንድ ትልቅ መሰረት ጥለዋል ማለት ይቻላል::

ልዩነት መኖሩን አውቆና ልዩነቶቹ ደግሞ መሰረታዊ ከመሆናቸው የተነሳ ሁሌም አብረህ የምትኖራቸው እንጂ ለአንዴና ለሁሌም የምትፈታቸው አይደሉም ብሎ፤ ልዩነቶችን ከሚፈራ ሳይሆን ከተቀበለ፤ ልዩነቶችን እንደ ችግርና እንቅፋት ሳይሆን በበጎ ላየው እንደ መልካም እድልና የባህል ዲታነት ከወሰደ ግንዛቤ መነሳት ማለት አብሮነትን መዘንጋት፤ ወይንም ለጋራ ህይወታችን በቂ ትኩረት አለመስጠት አይደለም:: አብሮነታችንን ካልተቀበልንና የወደፊት እጣ ፈንታችን በጅጉ የተቆራኘ መሆኑን ከልባችን ካላመንን ስለተባበረ ትግል በተግባር ማውራት ከንቱ ነው :: ትግሉም የጋራችን የሚሆነው እኮ በጥሩ መሰረት ላይ ልንገነባ የምንፈልገው የጋራ ቤት አለን ብለን ስናምን ነው:: ለዚህ ነው በኛ እምነት የመጀመሪያውን ራዕይ ከመጋራት ባልተናነሰ ባንድም ሆነ በሌላ መንገድ ክፉኛ የተሳሰርን፤ ለበጎም ሆነ ለክፉ ህይወታችን የተቆላለፈ፤ የአንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ መሆናችንን መቀበል ሁለተኛውና እጅግ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ነው የምንለው:: ይህ በጋራ ለመታገል ለሚደረግ እንቅስቃሴ ሁለተኛው አስፈላጊ ምሰሶ ነው:: ሁለቱ አስፈላጊ ሁኔታዎች ግን ለየብቻቸው ካላቸው አስፈላጊነት ባሻገር አንዱ ለሌላው ተግባራዊነት እጅግ አስፈላጊ ነው:: በኛ እምነት ልዩነትን ያላወቀና ያላከበረ ስርዓት ዴሞክራሲያዊ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን አንድነትን ለማስጠበቅና አንድነቱን በዘላቂነት ለማስቀጠል አይቻለውም:: ልዩነትን በመደፍጠጥ የሚመጣ አንድነት እንደማይኖር ከሌላ አገር ታሪክ ሳይሆን ከራሳችን የቅርብ ጊዜ ታሪክ በደንብ የተረዳነው ይመስለኛል:: እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን የመሰለ የአንድነት መድሀኒት የለም:: በዚያው ልክ ግን የብሄር መብቶችን በእውነት ለማስከበር፤ በቋንቋ መናገርንና ባህልን ማክበርን ብቻ ሳይሆን ሀቀኛ ራስን ማስተዳደር በተግባር እንዲኖር በዴሞክራሲያዊ መርህ ላይ የተመሰረተ አገራዊ አንድነት አስፈላጊ ነው:: ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ሁኔታ ሁለቱ በኛ እምነት ያንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው::

እነኝህ ሁለት አስፈላጊ እምነቶች መኖራቸው ምንም ነገር አብሮና ተባብሮ ለመስራት፤ የተጣመረ ድርጅታዊ ቅርጽ ይዞም ሆነ እንዲሁ ስስ በሆነና የጋራ አላማ በሚያገናኛቸው የተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ ያተኮረ ስራም ለመስራት አስፈላጊ ነው:: የተቀናጀና ሁለንተናዊ ትግሉን በተጠናከረ ድርጅታዊ መዋቅር አሰባስቦና በጋራ አመራር ስር መርቶ ከዳር ለማድረስ ግን እነኝህ የጋራ ራዕዮች በቂ ኣይደሉም:: ከዚያ በላይ ብዙ መሟላት ያለባቸው ነገሮች ኣሉ:: ይህን ለመስራት በጋራ የሚሰባሰቡ ድርጅቶች በእያንዳንዳቸው ድርጅቶችም ውስጥ ሆነ አብረዋቸው ከሚሰሯቸው ድርጅቶች ጋር እስከ ትግሉ መዳረሻ የሚያዘልቅ ከፍተኛ መተማመን ሊኖራቸው ይገባል:: አንዱ የአንዱን መሰረታዊ እምነት ጥያቄ ውስጥ እያስገባ ረጅም ጉዞ አብሮ መጓዝ አስቸጋሪ ነው:: አንዱ በአንዱ ትከሻ ላይ ቆሞና ተረማምዶ የሚያገኘው የተለየ ጥቅም አለ ብሎ በውስጡ እያሰላ ውጤታማ ትብብር ፈጽሞ አይቻልም:: መተማመን ደግሞ ከእውነተኛነት ጋር የተቆራኘ ነው:: የሚነግረኝ ነገር እውነት መሆኑን የምጠራጠረው ሰው የሚለኝን ነገር ተማምኜ ምንም አይነት ተግባራዊ እርምጃ አልወስድም:: አብሮኝ ለሚሰራ ሰው ቀናነት ከሌለኝና እሱም ለኔ ቀና አመለካከት ከሌለው ግንኙነታችንን የሚያስሩ አስር ውሎች ቢኖሩንም  አመርቂ የሆነ ስራ በጋራ ልንሰራ አንችልም:: በጋራ ለገባናቸው ውሎች፤ ለተስማማንባቸው የአሰራር ሂደቶች፤ እያንዳንዳችን በግልም ሆነ በድርጅት ለወሰድናቸው ሀላፊነቶች ተዓማኒ ካልሆንን፤ በእያንዳንዱ ሁኔታ ላይ አንዳችን የአንዳችንን የውስጥ ግፊትና ፍላጎት (motive) እየጠየቅን አይደለም እንደዚህ አይነት አድካሚና ብዙ መስዋዕትነት የሚጠይቅ ስራ፤ መለስተኛ ሱቅ እንኳን በውጤታማነት ባክሲዮን ልናካሂድ አንችልም:: ይህ እንግዲህ በድርጅቶች ውስጥ ያለን ባህልና በድርጅቶች ውስጥ የተሰባሰቡ አባሎችን ጠንካራ ስነምግባር ይጠይቃል:: ይህ ደግሞ በሰፊውና በቀላሉ የሚገኝ እሴት እንዳልሆነ ሁላችንም የምንገነዘብ ይመስለኛል::

የተባበረና ውጤት ተኮር ስራ ሌላ የሚፈልገው ነገር ደግሞ ጠንካራ የስራ ባህል ነው:: ከመነሻው ይህ ስራ በወሬ የሚከወን ሳይሆን በጠንካራና እልህ አስጨራሽ ስራ ብቻ ዳር የሚደርስ ስራ ነው:: ፍላጎት ስላለ ብቻ ስራ ይሰራል ማለት አይደለም:: ከጠንካራ ፍላጎት በተጨማሪ የስራ ችሎታና ተነሳሽነት ይጠይቃል:: ይህን ችሎታም ሆነ ባህል ደግሞ ሁሉም ድርጅቶች በእኩል ኣዳብረውታል ማለት አይደለም:: ጠንካራ የስራ ባህልና ችሎታ የሌለው ሀይል ችሎታውና ተነሳሽነቱ ካለው ሀይል ጋር በሚጣመርበት ጊዜ ስራውን ከመጥቀም ይልቅ የሚጎዳበት፤ እንደሁኔታው ደካማው የሚጠናከርበት ሳይሆን ጎበዝ ሰራተኛው የሚሰንፍበት ወይንም ስራውን በተገቢው ሊሰራ የማይችልበት ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል:: ይህ ከሆነ ደግሞ መተባበሩን ትርጉም የለሽ ያደርገዋል:: ለዚህ ነው የማንኛውም ተግባራዊ የትብብር ሂደት ጥንካሬና ዘላቂነት የሚለካው በመሰባሰብና አብሮ በመስራት የሚገኘው ውጤት ድርጅቶቹ ብቻቸውን ቢንቀሳቀሱ ከሚገኝው ድምር ውጤት እጅግ የላቀ ሆኖ በመገኘቱ ወይም ባለመገኘቱ ነው:: አለበለዚያ ትብብር መፍጠሩ በራሱ ግኝት ይሆንና ትብብሩ ያስፈለገበት ዋና ግብ የትብብሩ ሰለባ የሚሆንበት ውጤት አልባ መዳከር ውስጥ ይከተናል::

ባለፉት 40 ግድም አመታት በአገራችን የተለያዩ የፖለቲካም ሆነ የሲቪክ ድርጅቶች በተለያዩ ምክንያቶች፤ ለተለያየ አላማ ተቋቁመዋል:: ወያኔ ስልጣን ከያዘ በኋላማ እንደ አሸን ፈልተዋል ማለት ይቻላል:: በወያኔ ቅኝት የሚዘፍኑትንና እሱው ጠፍጥፎ የሰራቸውን እንኳን ከስሌቱ ብናስወጣ፤ ባንድ መልኩም ሆነ በሌላ የወያኔ ተቃዋሚ የሚባለው ሀይል እንኩዋን ቢያንስ ከ50 በላይ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ሳይኖሩት አይቀርም:: በዚህ ላይ ከተቃዋሚው ጎራ ሊሰለፉ የሚችሉ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችን ከቆጠርን ቁጥሩ የትየለሌ ነው:: እነኝህ ድርጅቶች ከላይ በጠቀስናቸው ሁለት ግቦች ዙሪያ ሙሉ ለሙሉ የሚስማሙ ናቸው እንኳን ቢባል በድርጅታቸው አወቃቀር፤ በውስጥ ድርጅት ባህላቸው፤ ባሰባሰቡት አባላት አይነት፣ ብዛትና ጥራት፤ በተላመዱት ያሰራር ዘይቤና በመሪዎቻቸው ይዘትና አሰያየም የተለያዩ ናቸው:: እነኝህን ሁሉ ድርጅቶች በአንድ መድረክ ስር በእኩልነት አሰባስቦና እኩል ሀላፊነት ሰጥቶ፤ ጊዜው በሚጠይቀው ፍጥነት የጋራ ውሳኔ እየሰጠና ይህንንም ውሳኔ ወጥ በሆነ አመራር ለመተግበር በሚችል መልኩ የተዋቀረ ተግባራዊ ትግል ማኪያሄድ ይቻላል ብሎ የሚያምን ብዙ ሰው ያለ አይመስለኝም:: የተጣመረ የጋራ ትግል ያስፈልጋል የሚለውና በአብዛኛው ህዝባችን ዘንድ ተቀባይነት ያለው አመለካከት ተግባራዊ ውጤት እንዲያመጣ ከአስፈለገ ከነኝህ ድርጅቶች ውስጥ ከላይ የጠቀስናቸውን የጋራ ራዕይ የሚጋሩ፤ በትግሉ እስትራቴጂና ስልታዊ አካሄድ ዙሪያ የተቀራረበ አመለካከት ያላቸው፤ የስራ ባህላቸውና ተነሳሽነታቸው የሚቀራረብ፤ እርስ በርስ ለመተማመን የሚያስችል የባህልና የስነምግባር እሴቶች የሚጋሩ ወይንም ቢያንስ በሂደት ለመገንባት ጽኑ ፍላጎት ያላቸው ሀይሎች መሆን አለባቸው:: በሌላ አነጋገር የተቀናጀ ስራ ለመስራት የሚያስችል መናበብ ያላቸው ሀይሎች መሆን ይገባቸዋል:: አለበለዚያ አንዱ የአንዱን ድክመት የሚሸፍን፤ አንዱ ሲወድቅ አንዱ ደግፎ የሚያነሳው በአንድ አላማ ስር የተሰለፈ ጠንካራ ሀይል መሆኑ ቀርቶ አንዱ የአንዱ እንቅፋት የሚሆንበት፤ አንዱ ሌላውን የሚጠብቅበት፤ ችሎታ ያላቸው ትግሉን በችሎታቸው የሚያግዙበት ሳይሆን በምቀኝነት አንዱ ሌላውን የሚጎትትበት ቤት ሆኖ ሁሉም ተያይዘው የሚወድቁበት አሳዛኝ ሁኔታ ይፈጠራል:: አሁን ያለንበት አስቸጋሪ አገራዊ ሁኔታ ደግሞ በፍጹም ይህንን የሚፈቅድ አይደለም::

ተግባራዊ ስራ ለመስራት የሚችሉና ስራ ለመስራት የሚያስፈልገውን አስፈላጊ ባህል የሚጋሩት ሀይሎች ጠንካራ የጋራ መዋቅርና አመራር ፈጥረው በመንቀሳቀስ ወደ ውጤቱ ያስጠጉናል ማለት ግን ከእንዲህ አይነት ድርጅታዊ መዋቅር ውጪ ያሉት ሌሎች የፖለቲካ ሀይሎች ለጋራ ትግሉ ስኬት የራሳቸው አስተዋጽኦ አያደርጉም ማለት አይደለም:: አንዳንድ ድርጅቶችና ተቋሞች ከሌሎች ጋር በድርጅታዊ መዋቅር ውስጥ ሆነው ከሚሰሩ በራሳቸው ድርጅታዊ ባህል ውስጥ ሆነው የሚሰሩት ለትግሉ የበለጠ ጥቅም ሊሰጥ ይችላል:: በምንም አይነት ድርጅት ውስጥ ሳይገቡ በግላቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ግለሰቦች ያሉትን ያክል:: አሁን ያለንበት ሁኔታና የገጠመን ባላንጣ ደግሞ ትንሽም ቢሆን አስተዋጽኦ ለማድረግ ከሚችልና ከሚፈልገው ሁሉ ያንን አስተዋጽኦ ይፈልጋል:: ከእንደነኝህ አይነት ግለሰቦችና ድርጅቶች ጋር በድርጅት ደረጃ የተቋቋመው ትብብር ቢያንስ አንዱ ባንዱ ላይ እንቅፋት እንዳይሆን፤ ወይንም በተወሰኑና በግዜ በታጠሩ ልዩ ስራዎች ዙሪያ፤ ወይንም ደግሞ ትግሉ የሚሄድባቸውን የተለያዩ ወሳኝ ደረጃዎች ያስቀመጠና በነኝህ ወሳኝ ደረጃዎች ደግሞ ሁሉን የዴሞክራሲ ሀይሎች ሊያሳትፉ በሚችሉ ሂደቶች ዙሩያ ስምምነት ፈጥሮ ስስ በሆነ ግንኙነት ትብብሩን መቀጠል ይቻላል:: በዚህ ዙሪያ በምንም አይነት መፈቀድ የሌለበት ጠባብ ድርጅታዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ተብሎ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንፈልጋለን በሚሉ ሀይሎች መሀል አላስፈላጊ እንካሰላንቲያ ውስጥ መግባትና በዚህም ወያኔን በእጅ አዙር መጥቀም ነው:: ሌላውን የወያኔ ተቃዋሚ ሀይል በመዝለፍ፤ የሀሰት ክስ በማቅረብ፤ ወይንም በአጠቃላይ እሱን በማዳከምና ከተቻለም በመጣል እኔ እንደ ተቃዋሚ ድርጅት እጠቀማለሁ የሚል ከንቱ ስሌት ከብዙ ተመክሮ ታይቶ ፋይዳ የሌለው ስሌት መሆኑ ግልጽ ሆኖል:: ስለዚህ ለሌላው ተብሎ ሳይሆን ለራስ ድርጅት ውጤታማነትም አይበጅምና እርግፍ አድርገን ልንተወው ይገባል:: ወያኔን በእጅ አዙር በመጥቀም የሚገኝ የተቃውሞ ድርጅት ጥቅም የለም!!!

ጥምረታችንና በጀነራል ከማል ገልቹ የሚመራው ኦነግ የወሰደው አቋም ለተባበረ ትግል የከፈተው እድል፣

ይህን ትግል ውጤታማ ለማድረግ ምን አይነት የድርጅቶች ህብረት በሚለው ጉዳይ ላይ በጥቅሉ ይህን ያህል ከአልኩ ዛሬ እዚህ ስብሰባ ያመጣንን በጀነራል ከማል ገልቹ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አካል በቅርቡ የወሰደው ታሪካዊ አቋም ውጤታማ ለሆነ የተባበረ ትግል የሚኖረውን አስተዋጽኦ በሚመለከትና ጥምረታችን ከፊታችን የተደቀነውን፤ ትግሉን በተባበረና ወጥ በሆነ የጋራ አመራር መርቶ ከዳር ለማድረስ የሚያስፈልገውን የተወሳሰበ ስራና ሂደት በሚመለከት ያለንን ያላለቀለትና በየጊዜው ከተመክሮ እያዳበርን እየሄድን ያለውን አመለካከት በአጭሩ አቅርቤ ላብቃ::

ከላይ በጥቅሉ እንዳቀረብኩት ትብብራችን የተጣመረ ትግልን በሚመለከት ያለው አመለካከት እስትራቴጂካዊ ነው:: አሁን ከፊታችን የተደቀነውን ወያኔን የማስገደድ ብሎም የማስወገድ ትግል ይጠቅማል ከሚል ጊዜያዊ ስሌት በመነሳት ሳይሆን ዘላቂ የሆነውን ልንደርስበት የምንፈልገውን “ኢትዮጵያን እውነተኛ ፌደራላዊና ዴሞክራሲያዊ” ለማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለን ስለምናምን ነው:: ይህ እስትራቴጂካዊ ስሌታችን ደግሞ በምንም አይነት የአጭር ጊዜ ታክቲካል ጥቅም ለሚያስገኝ ግን ለስትራቴጂካዊ ግባችን እንቅፋት በሚሆን እርምጃ አንለውጠውም:: ይህን አካሄዳችንን ሁሉም ሰው (ወዳጅም ባላንጣም)  በቅጡ እንዲገነዘበው እንፈልጋለን:: በዚያው ልክ ደግሞ ከእኛ ቁጥጥር ውጭ የሆኑ ብዙ ክስተቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉና እኛ የምንወስናቸው ውሳኔዎች እነኝህን ከቁጥጥራችን ውጪ ያሉ ክስተቶችን እንዳሉ ተቀብለን (ልንቀይራቸው ስለማንችል) ያንን ውጫዊ ክስተት ወደ እስትራቴጂክ ግባችን ለመሄድ ለምናደርገው ጉዞ ቢቻል እንዲያግዘን፣ ባይቻል ግን በጣም እንቅፋት እንዳይሆነን፣ ለማድረግ የሚያስችሉ ውሳኔዎች እየወሰንን መሄድ ነው:: በጃፓን የተከሰተውን ሱናሚ የጃፓን መንግስት ሊያስቆመው አይችልም:: ሱናሚው ሊያስከትል የሚችለውን  ጥፋት ግን (ለምሳሌ የኒውክሌር ተቋማትን በበቂ የአደጋ መከላከያ አጠናክሮ መስራት) የሚቀንስ እርምጃ መውሰድ እንደሚችለው ማለት ነው::

ይህን የምለው ያለ ምክንያት አይደለም:: እነጀነራል ከማል ገልቹ ውሳኔያቸውን ካሳወቁ ጀምሮ በተለይ በአንዳንድ የኦሮሞ ወንድሞቻችን ዘንድ እጅግ የተሳሳቱና ከእውነት የራቁ ክሶች በድርጅታችን ላይ ሲሰነዘሩ ስለምንሰማ በዚህ አጋጣሚ እነኝህን ስህተቶች ማጥራት ወደፊት ለሚደረገው ትግል ጥቅም ይኖረዋል ከሚል እምነት ነው:: እነኝህ የሚሰነዘሩት ክሶች ሀሰት መሆናቸው እየታወቀ ግን ደጋፊዎችን በጊዜያዊ ስሜት ለማነሳሳት ይጠቅማል በሚል ስሌት የተደረገ ከሆነ፤ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት እንደዚህ ኣይነት ስሌቶች ወንዝ አያሻግሩምና ይቅርብን እላለሁ:: በጥቅሉ እነኝህ ክሶች ሁለት አይነት ናቸው:: የመጀመሪያው ይህን በኦነግ ውስጥ የተፈጠረውን ችግርና ኣዲሱን አቋም እኛ የፈጠርነው ወይንም እኛ የገፋፋነው ተደርጎ የሚቀርበውና በቀላሉ እውነት ወይም ሀሰት በሚል በመረጃ ተደግፎ ሊመለስ የሚችለው ነው:: ሁለተኛው ደግሞ እኛ ከዚህ መከፋፈል እንጠቀማለን ብለን የምናስብ ተደርጎ የሚቀርበው የኛን የውስጥ እምነት ካለመረዳት የሚመጣው ክስ ነው::

በመጀመሪያው ላይ መልሳችን አጭርና የመልሳችንን ትክክለኛነት ለመመዘን ደግሞ የሚያስፈልገው ማስረጃ በቀላሉ የሚገኝ መሆኑን ማሳወቅ ነው:: ግንቦት7ትም ሆነ ጥምረታችን በኦነግ ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈል እንዳይኖር፤ ከተፈጠረም በኋላ ችግሩ በኦሮሞ ሽማግሌዎች እንዲፈታ ምን ያህል ጥረት እንዳደረግን በዚህ ግጭት ዙሪያ ዋና ተዋናዮች የነበሩት ሁሉ የሚያውቁት ነው:: ብዙዎቻችሁ እንደምታስታውሱት የኦሮሞ ሽማግሌዎች ችግሩን ፈተውታል የሚል አጭር መግለጫ ባወጡ ጊዜ “ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ” እየተባለ “በአንድነት ሀይሎች” እስከሚሾፍብን ድረስ እርቁን በመደገፍና የነሱ መታረቅ ለጋራ ትግላችን የሚኖረውን ጥቅም በማተት ረጅም መግለጫ ያወጣነው እኛ ነን (ይህ በማርች 18፣2011 የወጣው መግለጫ አሁንም የጥምረቱ ድረገጽ ላይ ኣለ)::  እርቁ ደፈረሰ ሲባልም ከሽማግሌዎቹ አንዳንዶቹን እርቁ እንዳይፈርስ አጥብቀው እንዲሰሩ ከመማጸን ኣልፈን ምናልባት በወዳጅነት ሁለቱንም ይቀርቧቸዋል ያልናቸውን ሶሶተኛ ወገኖች እርቁን እንዲገፉ ያላደረግነው ጥረት የለም:: ይህንን ደግሞ ሁሉም ወገኖች ያውቁታል::

በርግጥ እንደ ድርጅት ከሁሉም ወገኖች ጋር ግንኙነት ነበረን:: ይህን ደግሞ በድብቅ ሳይሆን በግልጽ ለሁሉም ወገኖች ነግረን ያደረግነው ነው:: ይህን ደግሞ ወደፊትም የምንቀጥለው ነው:: እኛ እንደ ድርጅት ያንድ ማህበረሰብ ወኪል ይህ ወይንም ያንኛው ድርጅት ነው የሚል መራጭ አይደለንም:: ይህን ማድረግ የሚችለው እንወክልሀለን የሚሉት ህዝብ ብቻ ነው:: ይህን ደግሞ ተቀባይነት ባለው ደረጃ ማድረግ የሚችለው በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ያድርጅት ሲመረጥ ብቻ ነው:: እስከዚያ ድረስ እኛም ሆንን ሌሎች ድርጅቶች እኛ ብቻ ነን የህብረተሰቡ ወኪል ብለው ለመናገር የሚያስችላቸው የህግም ሆነ የሞራል መሰረት የለንም:: ትግላችንም ይህንን ውክልና በተገቢው መንገድ እንዲያገኙ ነው:: እስከዚያው ድረስ ግን ቢቻል ሁሉም ባንድ ላይ ተሰባስቦ፤ ካልተቻለ በስራ የሚስማሙትና የሚተማመኑት ጋር ትብብር እየፈጠሩ፤ ካልሆነም ሁሉም በበኩሉ ይህ የውክልና ስርዓት እንዲፈጠር በሚያደርገው ትግል በአላማ እየተናበቡ ወደፊት መሄድ ነው የሚመረጠው:: የኦሮሞም ሆነ ሌሎች በብሄር ላይ የተመሰረቱ ትግሎች በኢትዮጵያ አንድነት ዙሪያ ከተሰበሰቡ ሀይሎች ጋር አብረው መስራት አለባቸው፤ ለዚህም አቋማቸውን ለማስረዳት የጋራ ስብሰባዎችን ማድረግ ይጠቅማል ብለን ስብሰባዎችን ስናዘጋጅ ሁሉንም ወገን ነበር ለስብሰባዎች የምንጋብዘው:: አንደኛው ካለ ሌላው አልገኝም የሚሉ ችግሮች እንኳን ሲገጥሙን ባንደኛው ስብሰባ ላይ አንዳችሁ በሌላው ሌላኛችሁ ተገኙ ይህንን የውይይት ሜዳ አትተዉት፤ እንደዚህ አብሮ ከመወያየትም በውስጣችሁ ያለውንም ልዩነት ማጥበብ ትችላላችሁ እያልን ምን ያክል ስንለምን እንደነበረ ሁሉም በአመራር ላይ የነበሩ ሰዎች ያውቁታል:: ስለዚህ በውስጥ ያሉ አብሮ የመስራት ችግሮች ካሉ እነሱን አጥርቶ ማወቅና መፍትሄ መፈለግ ይጠቅም እንደሆን እንጂ ችግሮችን በሙሉ “ባዕድ” ለተባለ ሀይል ኣሳልፎ ለመስጠት መሞከር ወደመፍትሄው አያስጠጋም:: በእውነት ላይ ያልተመሰረተ ትንተና፤ በዚያ ትንተና ላይ ተመሰርቶ የሚወሰድ እርምጃ (ፕሮፓጋንዳን ጨምሮ ) ግፋ ቢል ጊዜያዊና ግልብ ጥቅም ያስገኝ እንደሆነ እንጂ ዘላቂ ትርፍ የለውም:: በውሸት ያሰባሰቡት ሀይልና ደጋፊ እውነቱ ሲገለጽ ይተናል:: እንደ አገር የውስጥ ችግሮቻችንን ፊትለፊት ከመጋፈጥና መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ “በባዕዳን የተፈጠሩና፤ የባዕዳን አላማ ለማሳካት” የሚደረጉ ናቸው እያልን በድፍኑ እየፈረጅን ቅንጣት ታክል መፍትሄ አላመጣንም:: ቢያንስ ከዚያ መማር ይገባናል::

ሁለተኛው ክስ ግን መሰረታዊ አመለካከታችንን የሚመለከት ነው:: የክሱ ምንጭ እንደሚመስለኝ ፖለቲካችን በ1960 ዎቹ የአብዮት ወቅት ከነበረበት አመለካከት፤ በተለይም “ከኔ የተለየ ሁሉ ጠላቴ ነው”፤ በአመለካከት የተለየኝ ሁሉ እኔን ለማጥፋት ወይንም ለማዳከም ነውና የሚፈልገው ቀድሜ ማጥፋት ወይንም ማዳከም አለብኝ፤ የተለያየ አመለካከት ባላቸው ሀይሎች መሀል ምንም የጋራ ጥቅም ብሎ ነገር የለም ከሚለውና ለረጅም ጊዜ ከተጣባን፤ ሁሌም ፖለቲካን ድምሩ ዜሮ የሆነ ስሌት ብቻ አድርጎ የሚያይ አመለካከት የወለደው ነው የሚመስለው:: የዚህ አይነት አመለካከት የተጠናወተው ፖለቲካ ደግሞ  ለመተባበር፤ ለሰጥቶ መቀበል፤ ባጠቃላይ ለዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ የማይመች ከመሆኑም ባሻገር፤ በሀሰት የተሞላ፤ በጣም ብዙ ማጋነን የበዛበት፤ የሚለየውን ሰው ለመረዳት ቅንጣት ታክል ትዕግስት የሌለው፤ አላማው ሌላውን ለመጉዳት የሆነ፤ ብዙውን ጊዜ ትምህርትና እድሜም በቀላሉ የማያጸዳው በባህርዩም ቆሻሻ ፖለቲካ ነው:: በዚያ አብዮታዊ ፖለቲካ ጊዜ ያለፍን ሁሉ በደንብ የምናውቀው ነው:: ልንሄድበት ለምናስበው ፖለቲካ ደግሞ በፍጹም የማይበጅ ነው::

ክሱ ባጭሩ የሚለው “የነከማል ገልቹ ቡድን የፖለቲካ ኣቋሙን እንዲቀይር “የአንድነት ሀይሎች” የገፋፉትና ከቀየረም በኋላ በከፍተኛ ስሜት የተቀበሉት እነሱ ከኦነግ መከፋፈልና መዳከም እንጠቀማለን ብለው ስለሚያስቡ ነው፤ ወያኔ ኦህዴድን ፈጥሮ የኦሮሞ ህዝብ ወኪል ነህ ብሎ እንደሚጫወተውና ኦሮሞን ለመጨቆኛ እንደሚጠቀምበት ተቃዋሚ ነን የሚሉት እንደ ግንቦት 7 አይነት “አክራሪ የቀኝ ሀይሎች” ይህንን የነጀነራል ከማልንም ቡድን በሚቀጥለው ዙር ሊጠቀሙበት በማሰብ ነው”፤ በአጠቃላይም የኦሮሞ ህዝብ ጠንካራ ወኪል እንዳይኖረው ስለሚፈልጉ ነው” የሚል ነው:: በወያኔ ስር ጀነራል የነበረንና በአድርባይነት እንደሌሎች የወያኔ ጀነራሎች ገንዘብ ሰብስቦ፤ ህንጻ ሰርቶ ተንደላቆ መኖር የሚችል ሰው፤ ያንን ትቶ፤ እንደገና በአድርባይነት፤ ምንም ስልጣን ለሌላቸው ተቃዋሚ ሀይሎች መሳሪያነት ይውላል የሚለውንና “ግንቦት 7 የቀኝ ኣክራሪ” ነው የሚሉትን አይነት ትርጉም የሌላቸው ክሶች ትተን የክሱን መሰረታዊ ጭብጥ በሚመለከት ድርጅታችን ያለውን ኣቋም በግልጽ ላስቀምጥ::

እኛ እንደ ድርጅት ማንኛውም የወያኔ ተቃዋሚ ድርጅት በመዳከሙ እንጠቀማለን ብለን በፍጹም አናምንም:: የኦሮሞ ህዝብም ሆነ ማንኛውም በአገራችን ውስጥ ያለ ማህበራዊ ስብስብ በጠንካራና ችሎታ ባላቸው፤ የማህበረሰቡን ድጋፍ ባገኙ፤ የማንም ተለጣፊ ባልሆኑ ነጻ መሪዎቹ እንዲወከል እንፈልጋለን:: እንዲህ ኣይነት ጠንካራና በራሳቸው የሚተማመኑ የማህበረሰብ ወኪሎች ባሉበት በሚደረግ ድርድርና ሰጥቶ መቀበል ብቻ ነው፣ ይህች የምንፈልጋት አዲሲቱ ኢትዮጵያ የምትፈጠረው:: ወያኔን ለመጣል በሚደረገው የጋራ ትግል መሰባሰብ ያለበትም ሀይል ይህን አይነት የማህበረሰብ ድጋፍ የተጎናጸፈ ነው ብለን እናምናለን:: በኦነግ ውስጥ የሚኖር ክፍፍል እንወክለዋለን የሚሉትን የኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ሁሉንም ልጆቿን ያሰባሰበች፤ ከራሷ ጋር የታረቀች ዴሞክራሲያዊት አገር እንድትሆን የምንፈልገውን ሁሉ ነው የሚጎዳው::  ስለዚህ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ለተለያዩት የኦሮሞ ሀይሎች መሪዎች በግልጽ የነገርናቸውን እምነታችንን አሁንም በግልጽ በህዝብ ፊት ልድገመው:: ኢትዮጵያን እውነተኛ ፌደራላዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ የሚደረገው ትግል ግንባር ቀደም ሚና መጫወት የሚገባው የኦሮሞ ህዝብ፤ ይህንን አዲሲቱን ኢትዮጵያን የማዋለድ ሚናውን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር ሆኖ እንዲጫወት፤ የፖለቲካ መሪዎቹ በዚህ የጋራ ራዕይ ተሰባስበው፤ ሌሎች ጥቃቅን ልዩነቶቻቸውን ወደኋላ አድርገውና ወደፊት ህዝብ ዘንድ አቅርበው ለማስወሰን (ልክ እንደሌሎች የፖለቲካ ሀይሎች) ተስማምተው የጋራ ትግሉን በአንድነት ተቀላቀሉ:: እኛ እንደ ጥምረትም ሆነ እንደ ግንቦት 7 ኦነግ ወደዚህ አይነት የጋራ መስመር እንዲመጣ፤ በድርጅቱ ውስጥ ያለውን ልዩነት ለመፍታት የሚደረግን ማንኛውንም አይነት ጥረት (ከዚህ በፊት በኦሮሞ ሽማግሌዎች የተጀመረውን አይነት) በሙሉ ልባችን የምንደግፈው ብቻ ሳይሆን በዚህ ዙሪያ ማድረግ የምንችለው ምንም ኣይነት እገዛ ካለ ለማገዝ ወደኋላ የማንል መሆኑን በግልጽ ማስቀመጥ እፈልጋለሁ:: እመኑኝ ነው የምላችሁ የናንተን አንድነት በጽኑ እንፈልገዋለን:: ላለፉት ብዙ ወራቶች ባደረግናቸው የጋራ ውይይቶች በአመለካከት ደረጃ በጣም እየተቀራረብን የመጣነውንና ዛሬም በዚህ መድረክ ላይ አብረውን ያሉትን በጀነራል ከማል ገልቹ የሚመራውን የኦነግ ኣካል እንዲህ ኣይነት መቀራረብ፤ መስማማትና ታርቆም ባንድነት ለመሄድ የሚደረጉ ጥረቶች ካሉ ልባችሁን ከፍታችሁ እንድታዳምጡ፤ ከጊዜያዊ የጠባብ ድርጅት ጥቅም ባሻገር ለዘላቂው ውጤት አጽንኦት እንድትሰጡ፤ በክፍት አዕምሮም እንድትቀበሉት፤ ከዚያም ኣልፎ ግን ምንም አይነት ኣላስፈላጊ ንትርክና እንካ ሰላንቲያ ውስጥ ከወንድሞቻችሁ ጋር እንዳትገጥሙ እንማጸናችኋለን::

ይህን የምለው ግን ኦነግን ወይንም ከኦነግ ውስጥ ያለን አንድ አካል የኦሮሞ ህዝብ ብቸኛ ወኪል ነው ከሚል ቅዠት (illusion) ተነስቼ እንዳልሆነ በደንብ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ:: ይህንን የምለው በሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች ነው:: የመጀመሪያው ምክንያት ቀደም ብዬ የጠቀስኩት ነው:: ህዝብ በነጻነት ሳይመርጥ የሚገኝ ትክክለኛ (legitimate) ውክልና ብሎ ነገር የለም:: ኦነግም ሆነ እኛ ወይንም ሌላ ድርጅት ነጻና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እስካልተመረጠ ድረስ የዚያ ህዝብ ወኪል ነው ሊባል አይችልም:: ይህ ደግሞ ድርጅቱ አስር ግዜ ጠንካራ ቢሆን፤ ብዙ ኣባላት የሞሉት ቢሆን፤ ሰፊ የህዝብ ድጋፍ አለው ተብሎ እንኳን ቢገመት እውነትነቱ አይቀየርም:: በአባላት ብዛት እውነተኛ የህዝብ ውክልና የሚገኝማ ቢሆን አስገድዶና ገዝቶ ያከማቸው 5 ሚሊዮን አባል ኣለኝ ብሎ የሚደነፋው ኢህአዴግ የህዝብ ወኪል ይሆን ነበር:: ስለዚህ እውነተኛ የህዝብ ውክልና ትግላችን ዳር ሲደርስና፤ ነጻ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ የሚገኝ ነው:: እስከዚያው ድረስ ሁላችንም ይህ የህዝብ ውክልና እስኪገኝ ድረስ ይህ የህዝብ ውክልና የሚኖርበትን ስርዓት ለመመስረት የምንታገል ይብዛም ይነስም የተወሰኑ ደጋፊዎችና አባሎች ያሉን የተቃውሞ ትግል ተዋናዮች ነን:: ከዚህ ያለፈ ምንም ተጠሪነት (claim) የለንም::

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በእውነተኛ ምርጫ የሚገኝ ውክልና ቢኖር እንኳን ማንም ድርጅት የአንድ ማህበረሰብን ስሜትና ፍላጎት መቶ በመቶ የምወክል ወይንም በዚያ ማህበረሰብ ስም መናገር የምችል ብቸኛ ሀይል እኔ ነኝ የሚል ብዥታ ሊኖረው አይችልም:: ምክንያቱም በአንድ ማንነት (identity) ዙሪያ የተሰባሰበ ሀይል ያማንነት የሚነካቸው ሁሉ ተጠሪ ነኝ ሊል የሚችልበት ምንም አሳማኝ ምክንያታዊ መንገድ ስለሌለ ነው:: የዚህ ምክንያት ደግሞ የሰው ልጆች በተፈጥሮአችን የተለያዩ ማንነቶች ስላሉንና እነኝህ ማንነቶች ደግሞ አመለካከቶቻችንንም ሆነ ሰሜታችንን በተለያየ አቅጣጫ ስለሚጎትቱት ነው::

እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ በፖለቲካ አመለካከቴ የሶሻል ዴሞክራሲ ኣመለካከት እጋራለሁ፤ የኢኮኖሚክስ ባለሙያ ነኝ፤መምህር ነኝ፤ ጉራጌ ነኝ፤ የአርሴናል የእግር ኳስ ቡድንና የፊላዴልፊያ ኢግልስ እስፖርት ቡድኖች ደጋፊ ነኝ፤ ሙዚቃ አፍቃሪ ነኝ …ወዘተ. በነኝህ ሁሉ ማንነቶቼ ምክንያት የተለያዩ የተደራጁም ሆኑ ያልተደራጁ ማህበራዊ ስብስቦች ኣባል ነኝ:: እነኝህ ሁሉ በጋራ ሆነው የኔ ማንነት ገላጮች ናቸው እንጂ አንዱ ማንነቴ ብቻውን በምንም አይነት አይገልጸኝም:: ይህ አይነት የተለያዩ ማንነቶች ደግሞ ሁላችንም ላይ አሉ:: ስለዚህም ኣንድ አይነት ማንነት የሚጋሩ ሁለት ሰዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተለያየ አቋም ሊኖራቸው መቻሉ በፍጹም የሚገርም አይሆንም::  በመሆኑም  አንድ አይነት ድርጅት ውስጥ ብቻ ይሰባሰባሉ ማለት አይደለም:: ለምሳሌ አንድ ኦሮሞ ወገናችን የኦሮሞን የመብት ያለመከበር ችግር የሚፈታው ኦሮሞን ነጻ አገር በማድረግ ነው ብሎ ሊያምን ይችላል:: ሌላው ደግሞ በችግሩ ምንነት ላይ ተስማምቶ፤ የኦሮሞን ለብቻው መደራጀት ተቀብሎም የሚሻለው መንገድ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር አብሮ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ መታገል ነው ብሎ ሊያምን ይችላል:: አንዱ ይህንን መብት ለማስገኘት የሚበጀው አካሄድ በሰላማዊ መንገድ በወያኔ ህግ ስር ሆኖ መታገል ነው ብሎ ያምናል:: ሌላው ወያኔ ከጉልበት ሌላ አያውቅምና በሁለንተናዊ ትግል እንግጠመው ሊል ይችላል:: እንዲያውም ሌላኛው የለም መብቶች የሚባሉት ሁሉ ተከብረዋልና ከኢህኣዴግ ጋር አብሮ መስራት ይሻላል ሊል ይችላል:: ከዚህ ሁሉ ውጪ ደግሞ ኦሮሞ ተበድሎአል ብሎ አምኖ፡ ግን ኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ኢትዮጵያውያኖች እንደዚሁ ተበድለዋል ስለዚህም መፍትሄው ኦሮሞ ለብቻው መደራጀት ሳይሆን ህብረ ብሄራዊ በሆነ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ውስጥ መደራጀት ነው የሚበጀው ብሎ ያምናል:: እነኝህ አመለካከቶች ሁሉ የተለያየ አይነት አደረጃጀትን ሊጠይቁ በዚህም ምክንያት ኦሮሞዎች የተለያዩ  ድርጅቶች ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ:: አንደኛው አመለካከት ከሌላው የተሻለ ምክንያታዊ፤ የበለጠ ለመፍትሄ የቀረበ ነው የሚል ክርክር ልናደርግ እንችላለን:: ይህ ማለት ግን አንደኛው ከአንደኛው የተሻለ፤ የበለጠ፤ “ንጹህ” ኦሮሞ፤ ወይንም የኦሮሞ ብቸኛ ተቆርቋሪ ነው ማለት የሚቻል በፍጹም አይመስለኝም:: ኦሮሞዎች ለመብታቸውና ለእኩልነታቸው በታሪክም ሆነ አሁን በተለያየ ድርጅቶች ውስጥ ታግለዋል:: የድሮውን እንኳን ብንተወው ኦሮሞዎች አሁንም በኦብኮ ውስጥ፤ በኦፍዴን ውስጥ፤ በተለያዩ  የኦነግ ክፍሎች ውስጥ እንዲሁም ግንቦት 7ትን በመሳሰሉ በተለያዩ  ድርጅቶች ውስጥ በመስራችነት፤ በመሪነትም ሆነ በተራ ኣባልነት ደረጃ ይሳተፋሉ:: ከግንቦት 7 መስራች መሪዎችና በኋላም ከመጀመሪያው ጉባኤ ጀምሮ በችሎታውና በታታሪ ሰራተኛነቱ በጉባኤው የተመረጠው የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር ኦሮሞ ነው:: እንደ አንድ ህብረ ብሄራዊ ድርጅት ከሌሎች በኦሮሞነት ከተደራጁ ድርጅቶች ጋር በጋራ እንታገል ስንል በኦሮሞ ማንነት ውስጥ ብዙ ማንነቶች እንዳሉ አውቀን፤ በኦሮሞነት መደራጀት መብታችንን ለማስከበር የተሻለው መንገድ ይህ ኣይነቱ አደረጃጀት ነው ብለው የሚያምኑት ያላቸውን አመለካከት አክብረን፤ እውነተኛ የውክልና ስርዓት በመፈጠሩ ሁላችንም ስለምንጠቀም ለዚህ ግብ መተባበር ሁላችንንም ይጠቅመናል ብለን አምነን፤ እንፍጠራት የምንላት አዲሲቱ ኢትዮጵያ ሁሉም ማህበረሰብ ራሱ በነጻነት በሚመርጣቸው ጠንካራና በራስ መተማመን ባላቸው መሪዎቹ መወከሉ የበለጠ የጠነከረችና ከራሷ የታረቀች የተረጋጋች አገር ለመሆኗ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለን ከልባችን ስለምናምን ነው እንጂ፣ የኦሮሞን ህዝብ ጥቅም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጥቅም የማስከበርንና ለዚያም የመታገልን ሀላፊነት ከትከሻችን አውርደን አይደለም:: እኛ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ መብትና እኩልነት ቆመናል ስንል፤ ያለብን ሀላፊነት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ መሆኑን ላንድ አፍታም አንዘነጋም:: ለዚህ ነው ድርጅታችን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ክፍት የሆነው:: ስለዚህ ኦነግ አንድ ላይ ሆኖ ትግሉን እንዲቀላቀል፤ ልዩነቱን አስወግዶ በአንድነት እንዲቆም እንፈልጋለን፤ ለዚህም የተቻለንን እናደርጋለን ስንል፤ እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለኦሮሞ ወንድሞቻችን መብትና እኩልነት መታገል የኛም ሀላፊነትና ግዴታ መሆኑን በመቀበልም መሆኑን እንድትገነዘቡልኝ እፈልጋለሁ::

በነ ጀነራል ከማል ገልቹ አቋም መቀየር ዙሪያ በኛ ላይ የሚነሱትን ክሶች በሚመለከት ይህን ያህል ከአልኩ፤ ይህ ኣቋም በኦነግ አንድ ክፍል መወሰዱ በራሱ ያለውን ትልቅ ፋይዳ በተመለከተና ይህም ይዞ በሚመጣቸው የጋራ ትግል እድሎች ዙሪያ አንድ ሁለት ብዬ ላብቃ::

በነጀነራል ከማል ገልቹ የተወሰደው አቋም አሁን ባለው በተከፋፈለ መልኩ ሳይሆን ኦነግ በጋራ ወስዶት ቢሆን ኖሮ እጅግ የተመረጠ ይሆን እንደነበረ ከላይ ጠቅሻለሁ:: ይህም ሆኖ ግን እነጀነራል ከማል ገልቹ ከረጅም ጊዜ የውስጥ ድርጅት ውይይትና ክርክር በኋላ እዚህ ኣቋም ላይ መድረሳቸውና ከዚህ ኣቋም ጋርም በተያያዘ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ከሚታገሉ ሀይሎች ጋር በመሆን በጋራ ለመታገል መወሰናቸው በራሱ ትልቅ ግኝት መሆኑን ድርጅታችን ያምናል::  አስቸጋሪ በሆነው የአገራችን የፖለቲካ ምህዳር እንዲህ ኣይነቱን ስርነቀል አቋም በድፍረት መውሰድና ለተግባራዊነቱም ለመስራት ቆርጦ መነሳት በቀላሉ የማይታይ የፖለቲካ አርቆ አስተዋይነትንና ለሚያምኑበት እምነት ደፍሮ መቆምን የሚያሳይ ትልቅ እሴት ነውና ይህን ውሳኔ ለወሰኑት ወንድሞቻችን ያለንን ታላቅ አክብሮት በዚህ አጋጣሚ መግለጽ እወዳለሁ:: የዚህ ኣይነት አርቆ  አስተዋይነት ሌሎቹንም ወገኖቻችንን በዚህ ዙሪያ በጋራ እንዲሰለፉ ለማድረግ በሚደረግ ጥረትና አልፎም ትግሉን አስተባብሮና መርቶ የታለመለት ግብ ለማድረስ በሚያስፈልገው የትግል ውጣ ውረድ ላይ ከዋለ በርግጥም ወደነጻነታችን የምናደርገው ጉዞ ሊያጥር የሚችል መሆኑን አመላካች ነው::

ይህ አዲሱ ኣቋም ከላይ የተሳለጠ የጋራ ትግል ለማድረግ አስፈላጊ ናቸው ያልኳቸውን ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች ያሟሉትን ድርጅቶች ቁጥር ከመጨመሩም በላይ እውነተኛና ሁሉንም የአገሪቱን ክፍልና ማህበረሰባት ያካተተ ሰፊ ህዝባዊ የጋራ ትግል ለማድረግ ትልቅ እድል ከፍቶልናል:: ይህንን እድል በአግባቡ መጠቀም ደግሞ የሁላችንም ፈንታ ነው:: ሁላችንም እንደግለሰብም ሆነ እንደማህበረሰብ ተዋርደናል:: ይህን ውርደት ማስቆምና የሰው ልጅ መሆናችንን ማስረገጥ ለነገ የምንተወው የቤት ስራ አይደለም:: ትላንት መስራት የነበረብንን የቤት ስራ ባለመስራታችን ተከምሮ የጠበቀን የውርደት ተራራ ነው:: አይናችንን ጨፍነን በህሊናችን “እፍ” ስላልነው የሚጠፋ በምናባችን የፈጠርነው ቅዠት ሳይሆን ፊታችን ላይ ባሉት መስመሮች ላይ ታትሞ የተቀመጠ፤  በአስር አይነት ሳሙና ብንታጠበው የማይጠራ ሁሌም ፊታችንን በመስታወት ባየን ቁጥር መልሶ የሚመለከተን አሳፋሪ ቁስላችን ነው ውርደታችን:: ይህንን ውርደት ለማጥራትና እንደሰው ልጅ ቀና ብለን ለመሄድ ከፈለግንና ከቆረጥን ከፊታችን ብዙ ስራዎች ይጠብቁናል::

እነኝህን ስራዎች በምንፈልገው መልክና ይህን ትግል እንዲቀላቀሉ ከልባችን የምንፈልጋቸው ሀይሎች በሙሉ በአንድ ላይ የተባበረ ድርጅት ፈጥረው እስኪጀምሩት ድረስ ዝም ብለን የምንጠብቀው ኣይደለም:: ከላይ በዝርዝር እንደገለጽኩት በሁለቱ ራዕዮች ዙሪያ የሚስማማ ሁሉ በአንድ ጊዜ እንዲህ አይነት ትብብር ሊፈጥር ይችላል ማለት አይደለም:: ይህንን የሚችሉትና ለዚያ የተዘጋጁት ፈጥረውት ግን በሩን በደንብ ከፍተው፤ ሌሎችም እንዲህ አይነቱን ትብብር ለመቀላቀል ዝግጁ ሲሆኑ እነሱንም በእኩልነት ሊያሳትፍ የሚችል ክፍት የሆነ አወቃቀር ዘርግተው በየጊዜው የሚቀላቀሉትን እየጨመሩ ሌሄዱ ይችላሉ:: እስከዚያው ድረስ ግን ከሁሉም ጋር ያለው ውይይት እየቀጠለ፤ ሊያስማሙ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ እየተባበሩ ይህንን ከይሲ ስርዓት መቆሚያ መቀመጫ የሚያሳጣ ትግል ማካሄድ ጊዜው የሚጠይቀው አስቸኳይ የድርጊት መርሀ ግብር ነው::

ጥምረታችን ይህን እድል በአግባቡ ለመጠቀም ከላይ የተጠቀሱትን ለጋራ ትግል ኣስፈላጊ የሆኑ ሁኔታዎች ሊያሟላ የሚችል ሰፋ ያለ የትብብር እንቅስቃሴ ባስቸኳይ ለመጀመር ዝግጁ እንደሆንን መግለጽ እንወዳለን:: ወደዚህ አይነት የትብብር እንቅስቃሴ ስንገባ አስፈላጊ ናቸው ላልናቸው የጋራ አመለካከቶች፤ የድርጅታዊ ባህልና አሰራር እሴቶች ፍጹም ታማኝነታችንን ይዘን የምንገባ መሆኑን እንገልጻለን:: የዚህ አይነት ትብብር ጠንካራ መሰረት ላይ እንዲመሰረት ሰፋያሉ ውይይቶችና መግባባቶች የሚጠይቅ ነው:: ሌሎቹም ድርጅቶች ከራሳቸው ድርጅታዊ ታሪክና ባህል ላይ ተመስርተው ወደ ውይይቱ ይዘዋቸው የሚመጧቸው እሴቶች እንደሚኖሩና በመጨረሻውም ሁላችንንም የሚያስማማ የጋራ ሰነድ ብቻ ሳይሆን የምንስማማበት የአሰራርና የግብረገብነት መርህ እንደምንቀርጽ አንጠራጠርም:: ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት እንዲህ ኣይነት የጋራና የተደራጀ እንቅስቃሴ በተሰባሰቡት ድርጅቶች መሀል ከፍተኛ መተማመንን ይጠይቃል:: ለዚህም መተማመን እጅግ ኣስፈላጊ ነው ብለን የምናምናቸውን ከዚህ በታች የተጠቀሱትን ማለትም:

የተመደብነውን ስራ በአግባቡና በቅልጥፍና ለመስራት

አብረን የምንሰራቸውን ድርጅቶችም ሆነ ግለሰቦች በቅንነት ለመቀበል

በትብብር ስምምነቶቻችን መሰረት ለወሰድናቸው የጋራ ውሳኔዎች (ውሳኔውን ባንስማማበት እንኳን) ፍጹም ተገዢ እንደምንሆን፤ ትብብሩ የቆመለትን አላማ ከዳር ለማድረስ የምንቆጥበው ምንም ሀይል እንደሌለ

በምንም ኣይነት እንደማንዋሽ ወይንም ደግሞ በማስረጃ ባልተረጋገጠ ነገር ላይ በመነሳት ያልሆነ አታካራ ውስጥ እንደማንገባና

የምናምንበትን ነገር በግልጽ ለመንገር ወደ ኋላ እንደማንል

እንደጥምረት እነኝህን እሴቶች ይዘን የምንቀርብ መሆኑንና በማንኛውም ስራችን ለነኝህ እሴቶች ፍጹም ታማኝ እንደምንሆን ከወዲሁ በህዝብ ፊት ቃል እንገባለን::

ይህ ጊዜ በጣም ፈታኝ ጊዜ ነው:: አገራችን እጅግ ከባድ ችግር ውስጥ ነው ያለችው:: ታሪክ የሰጠውን ትልቅ እድል “ለሰላሳ ዲናር” የሸጠው የነመለስ ከይሲ ቡድን የማይቀረውን ውድቀቱን በሚሰራቸው እኩይ ስራዎች ባንድ በኩል እያፋጠነ በሌላ በኩል ደግሞ እሱ ትቶት የሚሄደው አገር “ለማንም እንዳይሆን” አፈራርሶት ለመሄድ ላይ ታች እያለ ነው:: እንዲህ አይነት የቀውስ ጊዜ ከመጥፎነቱ ጋር አብሮ ትልቅ እድልም ይዞ ይመጣል:: ይህን እድል አዲሲቷን ኢትዮጵያን ለማዋለድ ልንጠቀምበት ወይንም ከዚህ በፊት እንዳለፉት ሁለት እድሎች ልናበላሸውና በዚህም ምክንያት ችግሩ ተባብሶ በፍጹም የማንወጣበት ቀውስ ውስጥ አገራችን ልትገባ ትችላለች:: ጊዜው እውነተኛ የአዲስ አገር አዋላጅ አባቶችና እናቶች የሚፈልግበት ጊዜ ነው::

ለዚህም ነው ብልህ የሀገር መሪዎችና አባቶች በሚያስፈልጉበት በዚህ የቀውስ ዘመን ጥሩ ፖለቲከኛነት በቂ አይደለም የምለው:: ትልቁ ተስፋዬ፤ ያለፉትን ስህተቶች የተገነዘቡ፤ ከታሪክ የተማሩ፤ አለም አሁን ያለችበትን አጠቃላይ ሁኔታ በተገቢው የተረዱ፤ እነኝህን ስህተቶች ላለመድገም የማሰብ ችሎታው፤ የስራ ባህሉ፤ የሚጠይቀው የሞራል ስብእና ያላቸው መሪዎችና፤ ይህ ምህረት የማይገኝለት አስከፊ ታሪካዊ ስህተት እንደገና እንዳይፈጸም በተጠንቀቅ የሚጠብቅ፤ ያለንበትን አስቸጋሪ ሁኔታ የተረዳ፤ ከተራ ቲፎዞነት ያለፈ አዋቂና ንቁ ህዝብ ይኖረናል ብዬ ነው:: አገራችን ከዚህ ያነሰ ከኛ አትጠብቅም::

በጥሞና ስላዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ::

[1] ይህ ማለት የፖለቲካ ድርጅቶች በመሰረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ አቋም ሊኖራቸው አይገባም ወይንም አያስፈልግም ወይንም ለነኝህ ለሚያምኑባቸው መሰረታዊ እምነቶች መታገል የለባቸውም ማለት አይደለም:: እነኝህን አቋሞች ለህዝብ አቅርበው፤ አንዳቸው ከሌላቸው ያላቸውን የፖሊሲ ልዩነት በግልጽ አስቀምጠው የሚወዳደሩበት ጊዜው የምርጫ ጊዜ ነው:: አሁን ያለው ይህንን የመወዳደሪያ ስርዓትና ሂደት ፍትሀዊ የማድረግ ላይ ማተኮር እንዳለበት ለይቶ ለማቅረብ ነው::